Mar 22, 2012

የዋጋ ግሽበት የአገሪቱ ፈታኝ ችግር መሆኑን መንግሥት አመነ

መንግሥት ለዘይት ግዥ 1.5 ቢሊዮን ብር ገደማ ይደጉማል

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት በአገር ደረጃ፣ በመንግሥት፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ደረጃ ፈታኝ ችግር መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡ በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ተከትሎ መንግሥት የዋጋ ንረት የታየባቸውን መሠረታዊ ፍጆታዎች ከውጭ በማስመጣት በድጐማ ለኅብረተሰቡ ቢያቀርብም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈለገው ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ፣ አገሪቱ የገጠማትን ይህንን ፈታኝ ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ከሁሉም በላይ በዋጋ ግሽበቱ የሚጐዳው ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍሉ በመሆኑ፣ ችግሩ በአገር ደረጃ የሚካሄደውን ድህነትን የመዋጋት እንቅስቃሴ የሚፈታተን ሆኗል፡፡ መንግሥት በአገራቱ ውስጥ እጥረት የሚታይባቸው ሦስት መሠረታዊ የምርት ፍጆታዎች (ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር) ከውጭ አገር በመግዛት በአገር ውስጥ ማከፋፈል ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ችግሩ እየተባባሰ ከመሄድ ውጪ የመጣ ለውጥ የለም ብለዋል፡፡

የመሥርያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት አቶ ሱፍያን እንደገለጹት፣ መንግሥት ከውጪ ያስመጣቸው ምርቶች በጣም ቀልጣፋ የሆነ ግልጽነት የተላበሰ የግብይት ሥርዓት ተዘርግቶ ለኅብረተሰቡ ቢሰራጩ ኖሮ የዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀነስ ይችል ነበር፡፡

የዋጋ ግሽበቱን ይቀንሳል በሚል እምነት ባለፈው ዓመት ብቻ መንግሥት ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ 240 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ገዝቷል፡፡ በያዝነው ዓመት ደግሞ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የተገዛ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ያለው የ300 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጓጉዞ አገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት 30 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስንዴ እንደምታመርት የጠቆሙት አቶ ሱፍያን፣ መንግሥት ከወጪ ያስመጣው ስንዴ ታክሎበት በትክክል ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ቢሰራጭ የዋጋ ግሽበቱ ሊከሰት እንደማይችል ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ከ30 እስከ 35 ዶላር የሚሸጠው አንድ ኩንታል ስንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ለኅብረተሰቡ በ520 ብር፣ ለዱቄት ፋብሪካዎች ደግሞ በ560 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በድጐማ ገዝቶ ያስገባው ስንዴ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በዋና ዋና ከተሞችና በክልል ከተሞች መስተዳድር ጭምር የሚከፋፈል መሆኑን አቶ ሱፍያን አስረድተዋል፡፡ በአገሪቱ ከሚመረተው ስንዴ 70 በመቶ ያህሉ ለዱቄት ፋብሪካዎች ጥቅም የሚውል መሆኑን ጥናቶችን ጠቅሰው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ቁጥራቸውና የመፍጨት አቅማቸው የሚታወቀው የዱቄት ፋብሪካዎች ስንዴ እንዲያገኙና የፈጩትንም ስንዴ ለዳቦ ቤቶች የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡ ክልሎችም ራሳቸው በመረጧቸው አከፋፋዮች አማካይነት በወረዳና በዞን ከተሞች ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያከፋፍሉበት ዕድል መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡ የዘይት ግዥን በተመለከተም አንድ ሊትር ዘይት ከውጭ ገዝቶ አገር ውስጥ ለማስገባት 30 ብር የሚፈጅ መሆኑን፣ ለእያንዳንዱ ሊትር ዘይትም መንግሥት ከአራት እስከ ስድስት ብር ድጐማ እንደሚያደርግ አቶ ሱፍያን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የሚኒስትሩ መረጃ ሲሰላ በያዝነው ዓመት ብቻ ለሚከናወነው የ300 ሚሊዮን ሊትር ግዢ የምግብ ዘይት መንግሥት 1.5 ቢሊዮን ብር ይደጉማል ማለት ነው፡፡

የስኳር ምርት እጥረትም ቢሆን አሁንም ድረስ መፍትሔ የተገኘለት አይመስልም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የራሷን ፍላጐት ከመሸፈን አልፋ በዓመት ከ100 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ውጭ ትልክ እንደነበር ያስታውሱት አቶ ሱፍያን፣ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የስኳር ፍጆታ በመጨመሩ መንግሥት በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ስኳር ከውጭ አገር ገዝቶ ለማስገባት መገደዱን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ዘንድሮ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር መግዛቱንም አክለው ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ገበያ አንድ ኩንታል ስኳር ገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ሁለት ሺሕ ብር ይፈጃል፡፡ በአገር ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ ግን 1400 ብር መሆኑን አቶ ሱፍያን ይገልጻሉ፡፡ 

በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ መንግሥት የፍጆታ ምርቶችን ከውጭ እየገዛ በድጐማ ለኅብረተሰቡ የሚያከፋፍለው እስከ መቼ ድረስ ነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመሥራት የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ሱፍያን፣ ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ የውጪ ኩባንያዎች ሚና ምን ሊሆን ይችላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ በተለይም በጅምላ ንግድ ደረጃ የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ቢሆን የሚያስገኘው ጥቅምና የሚያስከትለው ስጋት ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ ለማጥናት በሚመለከታቸው መሥርያ ቤቶች ሚኒስትሮች የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተለያዩ አገሮች ልምድ ታይቷል፡፡ ሚኒስትሩ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገትን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተጠቀሰው በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 11 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ የኢንዱስትሪው ዘርፍም የ17.9 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

አቶ ሱፍያን ያቀረቡት የፌዴራል መንግሥት ፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት እንሚያሳየው፣ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ከታክስ ገቢ ብር 34,674.2 ሚሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች ብር 8,578 ሚሊዮን ብርና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ድጋፍና ዕዳ ቅነሳ ብር 1,944.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ የውጭ ሀብት ግኝትና አስተዳደርን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ወደ አገር ውስጥ ይፈሳል ተብሎ ከታቀደው 37.9 ቢሊዮን ብር ውስጥ በግማሽ ዓመቱ 20.4 ቢሊዮን ብር መገኘቱን የሚኒስትሩ ሪፖርት ያመለክታል፡

No comments: