Mar 22, 2012

መንግሥት በዋልድባ ገዳም የስኳር ልማት አላካሄድኩም አለ

ዳሙን በከበበው ዛሬማ ወንዝ ላይ ልማት እየተካሄደ ነው

በጥንታዊውና በአገሪቱ ካሉ ቅዱሳን መካናት በቀደምትነቱ የሚታወቀው የዋልድባ ገዳም ውስጥ ምንም ዓይነት የስኳር ልማት ፕሮጀክት አለማካሄዱንና የማካሄድ ዕቅድ እንደሌለው ያስተባበለው የኢትዮጵያ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን፣ በበርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም ሆነ በገዳሙ መነኮሳት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ያጣጣለው ‹‹ሌላ አጀንዳ ባላቸው ሰዎች የተነሳ ጥያቄ ነው፤›› በማለት ነው፡፡ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ከሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በወልቃይት፣ በአክሱምና በመቀሌ ያደረጉትን ስብሰባ አጠናቀው ትናንት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ በገዳሙ የቀረበውን ተቃውሞ አግባብ ባለው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር መሠረት ያልቀረበ፣ ይልቁንም የገዳሙ አንዳንድ መነኮሳት ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ያሰሙት አቤቱታ ትርጉም የሌለውና ተገቢ ያልሆነ በማለት ኮርፖሬሽኑ አጣጥሎታል፡፡

ነገር ግን የኮርፖሬሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የዋልድባን ገዳም ከከበቡት ወንዞች አንዱ በሆነው የዛሬማ ወንዝ ላይ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በትግራይ ክልል በሚገኘው ወልቃይት ወረዳ ላይ የሚካሄደው የስኳር ፕሮጀክት 25 ሺሕ ሔክታር መሬት የሸንኮራ አገዳ የሚለማበት ሲሆን፣ በቀን 10 ሺሕ ቶን አገዳ የሚፈጭ ፋብሪካ የሚገነባበት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ዛሬማ፣ ዱቁቆና ተከዜ ሸለቆ ሲሆኑ በተለይ የዛሬማ ወንዝ ለገዳሙ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ከኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ያገኘው መረጃ ግን ያንን የሚያስተባብል ነው፡፡

ወንዙን በመገደብ 3.8 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በመያዝ ለአገዳ ልማት እንደሚጠቀምበት ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፣ ከስኳር ፋብሪካው በዓመት 284 ሺሕ ቶን ስኳር እንዲሁም 26.8 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል ለማምረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአካባቢው 3,442 መኖርያ ቤቶች እንዲሁም 120 የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደሚገነቡ ሲጠበቅ፣ ሥራውን የሚያካሂድበትን ጽሕፈት ቤት በማይገባ ከተማ እንደከፈተ ታውቋል፡፡ እስካሁንም የግድብ ግንባታው ቁፋሮና እርሻውን፣ ፋብሪካውንና የመኖርያ መንደሮችን የሚያገናኙ መንገዶችም እተገነቡ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትናንትናው የዜና እወጃ ምሽት ላይ ስቱዲዮ ተገኝተው በገዳሙ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ በገዳሙና በስኳር ፕሮጀክቱ መካከል የስድስት ሰዓት ያህል ርቀት የሚገኝ ከመሆኑም በላይ በቅዱስነቱ ሳይነካ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን በታህሳስ ወር ላይ ገዳሙ በስኳር ፕሮጀክት ግንባታ ሳቢያ እየታረሰ፣ የቅዱሳን አባቶች አጽም እየፈለሰ፣ መቃብራቸው እየተደፈረና የጥርጊያ መንገድ እየወጣበት እንዲሁም ደግሞ ለፓርክነት እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ ከገዳሙ ውስጥ ከሚገኙ ልዩ ልዩ ገዳማት መፍትሔ እንዲሰጧቸው  በጹሑፍ መጠየቃቸው የሚታወስ ቢሆንም፣ አቶ ዓባይ ግን በመነኮሳቱ ያልቀረበ ጥያቄ በማለት ውድቅ ከማደረጋቸውም በላይ፣ ለገዳሙና ለሃይማኖት በመቆርቆር ሳይሆን በሰበቡ ተጠቅመው ተቃውሞ ለማስነሳት የፈለጉ ሰዎች ያነሱት ጥያቄ ነው ብለውታል፡፡

ጥያቄውን ያቀረቡት ግን የየገዳማቱ ተጠሪዎች እንደሆኑ ቢነገርም፣ የቤተ ክህነት አጣሪ ኮሚቴ በቦታው ተገኝቶ ማጣራቱንና ምንም ዓይነት ጉዳት በገዳሙ ላይ አይደርስም ማለቱ  ተነግሯል፡፡ ያም ሆኖ አቶ ዓባይ የሰዎች አጽም በክብር እየተነሳ እንደሚገኝ፣ በፕሮጀክቱ አካባቢ ተነሺ ለሆኑ ሰዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዛወሩ ከሕዝብ ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

No comments: