Jan 2, 2014

ታክሲ ውስጥ ጥቅሶች




‹ ክቡራን ተሳፋሪዎቻችን በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ አስተያየት፣ቅሬታ፣ትዝብት ወይም መሻሻል አለበት የምትሉት ነገር ካለ አንቀበልም!! መውረድ ይቻላል ››
     ድሮ ልጅ በነበርን ጊዜ የትምህርት መፅሐፍትን ማንበብ ጎበዝ ስለሚያስብለን ማንበብ አሁንም ማንበብ ነበር ስራችን ፡፡ የህፃንነት አህምሮ እንደጉልምሳ ብዙም ስለማያስቸግር የተሰጠውንና የገባውን ነው የሚቀበለው፡፡ በወቅቱ ከትምህርት መፃህፍት ውጪ ማንበብ ጊዜን አልባሌ ቦታ እንደማዋል እና ከዓላማ መሳቻ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከጥቂቶች በስተቀር በአብዛኛል ተማሪ አትኩሮቱ ደብተሩና ተያያዥነት ያላቸው መፅሐፍት ላይ ነበር፡፡ ምናልባትም ወላጆች ያሳደሩት ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ ይህን አልፎ ሁሉን አቀፍ ዕውቀት ያለው ተማሪ ማግኘት ብርቅ የነበረ ሲሆን ከተገኘም ጓደኛ ለማድረግ ተመራጭና ቅድሚያ ይሰጠው ነበር፤ እንደጎበዝ ይቆጠራል፡፡ ‹‹ እሱ ወይም እሷ ያላነበበው/ያላነበበችው መፃህፍት፤ ያላነበበው/ያላነበበችው ልቦለድ የለም ›› ይባላል፡፡
አንባቢ ነው የተባለውም ተማሪ መለያው ምልክቱ ደብተሩ በአባባሎችና ጥቅሶች ያሸበረቀና የደመቀ መሆኑ ነበር፡፡ የግሪኩ ፈላስፋ የተናገረው፣ የአረቦች አባባል፣የቻይናዎች አባባል፣ የኢትዮጵያውን ብሂል ወዘተ. . . ወዘተ . . . እየተባለ የተገኘው ይፃፋል፡፡ ምንጭ ይጠቀሳል፡፡ በሆነ አጋጣሚ ደብተሩን ያየ ወይም ያገኘ የተፃፈውን ፅሑፍ እና አባባል ኮርጆ ለራሱ ያደርገዋል፡፡ ታዲያ ማንም ተማሪ ጋር የሌለ ጥቅስና አባባል የሚፅፍ የሚናገር ‹‹ እሱ እኮ! ፤ እሷ እኮ !›› ይባልላቸዋል፡፡

ሌላው በትምህርት ቤት ህይወት ውስጥ የመለያያ ወቅት የሚባሉት ማለትም ተማሪዎች የሚለያዩበት 8ኛ፣10ኛ ወይም 12ኛ ክፍል ሊሆን ይችላል የሚዘጋጅ በተለምዶ ‹‹ ማስታወሻ ደብተር (Autograph) ›› ተብሎ የሚጠራ በዛ ያሉ ጥያቄዎችና መጠይቆች ያሉበት ለየት ያለ ማስታወሻ ይዘጋጅ ነበር፡፡ ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ጽጌሬዳ አበባ መሳል፣ግጥሞች መፃፍ የተለያዩ አስገራሚና አስቂኝ የሚባሉ ፅሑፎችን ማውጣት ዋና ስራ ነበር፡፡ ሁሉም አለኝ የሚለውን ይፅፋል፤ ያነበበውን ያካፍላል፤እራሱን ከሌሎች ጋር ያወዳድራል እንዲሁም እራሱን ሊያሳይ ይጥራል፡፡
ትንሽ ቆይቶ በአካልም በአስተሳሰብም እያደግን ስንመጣ ያ ሁሉ ነገራችብ ላይ መቀዛቀዝ ይታያል፡፡ ማንበብ ባይተው እንኳን  ለጥቅሶችና ለአባባሎች ያለን አትኩሮት ይቀንሳል፤ተፅዕኗቸውም  ይወርዳል፡፡ የዛሬን አያድርገውና በአንድ ወቅት በየመኖሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ በጥሩ የእጅ ፅሑፍ የተፃፉ አባባሎችን፣ ግጥሞችን ማየት የተለመደ ነበር፡፡ ብዙዎቹ አስተማሪና መካሪ ለሠዎች ቀና እንድንሆን፣ ወንጌልን የሚሰብኩና እግዚአብሔርን የሚማፀኑ ጥቅሶች ነበሩ፡፡ አንዳንዴም አሽሙሮችም አይጠፉበትም፡፡ በወቅቱ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማግኘት የሚቻለው በ‹‹ጠላ›› ወይም ‹‹አረቄ›› እንዲሁም ጠጅ ቤቶች አካባቢ ነበር፡፡ ምናልባት የሰከረን ለመምከር፣ ለማስተማር ወይም ብሶቱን ከፍ ለማድረግ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ የዋህ እና ደስ የሚል ጊዜ ነበር፡፡ታዲያ አሁንስ?
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በታክሲዎች ውስጥና ውጪ የምመለከታቸው ነገሮች የድሮ እና ያለፉትን ጊዜያቶችን ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ ግዜ በያንዳንዱ ታክሲ ውስጥ ጥቅስና አባባሎች ማየት እየተለመደ ከመምጣቱም በላይ እንደአንድ የመግባቢያ መንገድ መቆጠርም ጀምሯል፡፡ እንደያኔው ባይበዛም አስተማሪና ምክር አዘል ነገር በጥቂቱም ቢሆን አላቸው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የማሳቅ ይዘት ያላቸውና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለአንድ ለሚመለከተው አካል መልዕክትን  እንደ ማስተላለፊያ ዘዴ  ይጠቀሙበታል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊ እንዲሁም አሽሙራዊ ንግግሮች ከፍ ሲልም ስድቦች ያካትታሉ፡፡
አንድ ግለሰብ የሚፈልገውን መልዕክት በቀላሉ ለብዙሀን ለማስተላለፍ ካሻው ከፅሑፍ የተሻለ ነገር አማራጭ የለም፡፡ ሀሳባችንን፣ ስሜታችንን፣ ደስታችንን፣ ሀዘናችንን የሆነውን፣ ያሰኘነንን በመግለፅ ያለምንም ድካም የተፈለገውን ግብ መምታት ይቻላል፡፡ በተለይ በታዳጊ ሀገራት የታሻውን በቀላሉ ማግኘት ስለማይቻል መልዕክትን በቀላሉ ለሚመለከተው ክፍል ማድረስ ይከብዳል፡፡ በታክሲዎቻችንም ላይ የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ባለታክሲዎቹ ተሳፋሪዎቹ ጋር የያዙትን ግብግብ፡፡ ከተሳፋሪ ጋር ያላቸው ቀረቤታ እና ቅራኖ ያሰለቻቸው ነው የሚመስለው በሚመስል መልኩ የተለጠፉት ጥቅሶችና አባባሎች በሙሉ ሹፌሩን እና እረዳቱን የሚደግፉ፣ የሚያበረታቱ አትንኩን የሚሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በራስ ንብረት ላይ ሌላን ማሞገስ እና ማወደስ ሊከብድ ቢችልም የአብዛኛው ታክሲ ነጂዎች ስሜት ይመሳሰላል፡፡
ጥቂት ታክሲዎች ላይ ቢሆንም ተሳፋሪን የሚደግፉ ፅሑፎች ተመልክቻለሁ፡፡
ልክ እንደጊዜውና ወቅቱ የአባባሎቹ እና ጥቅሶቹ ይዘትና ዓላማ ይቀያየራል፡፡ ብዙዎቹ ግን የሚያተኩሩት መንግስትን የሚቃወሙ፣ የሚደግፉ፣ የሀገር ፍቅርን የሚገልፁ፣ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው፣ ስፖርት ተኮር ናቸው፡፡
እነዚህ የታክሲ ላይ ፅሑፎች ድሮ በየጠጅ ቤቱና ጠላ ቤቱ ከሚፃፉት የሚለዩባቸው አንዳንድ ነጥቦች አሉ፡፡ በዋናነት ግን የድሮዎቹ በቀጥታም ቢሆን መልካም ስሜትን ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡ ማለትም ጠንክሮ ስለመስራት፣ መበደል ቢኖር መቻልን፣ ክፉ አለመመኘትን፣ እና የመሳሰሉትን ትንሽም ቢሆን ፈሪሃ እግዚአብሔርን ይሰብካሉ፡፡ አንባቢውም ይሁን  ጠጪው  በዚሁ ቀለበት ውስጥ ያለ ነው፡፡ እንዳሁኑ ባይሆንም ቦታ ይሰጡታል አሁን የምናያቸው ግን ከላይ ያልኳቸውን ነገሮች ያካተተ ቢሆንም ብዙዎቹ ግን ‹‹እኔነት›› ስሜት አለባቸው፡፡ አትንኩኝ፣ ሂዱልኝ የሚሉ ብሶታዊ አንድምታ አላቸው ፡፡ መማረርና ጨለምተኝነት ይሰብካሉ፡፡በእርግጥ መልካም ሀሳብንም የያዙ አሉ፡፡
አንዳንዶችም የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር እንዳለ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ‹‹ለሚያልፍ ቀን ክፉ አትናገር›› . . . . ‹‹ የጌታ ፍቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን››. . . . ‹‹እግዚአብሔር ይፈርዳል›› . . .ወዘተ. . . መፅናናትን ተስፋ አለመቁረጥን አይዞን፣እንጠንክር ይላሉ፡፡ ፍርሃትን ፈጣሪዎች ናቸው፡፡በጊዜው ሁኔታ የፈጠረው እንደሆነ ባላውቅም ግን የሆነ የጎደለ ነገር እንዳለ ያሳያል፡፡

ስነፅሑፍ በጊዜያትና በትውልዶች መካከል በራሱ መንገድ የሚሄድና የሚለወጥ ጥበብ እንደመሆኑ የድሮን የአፃፃፍ ጥብበና ይዘት በዚህ ዘመን መጠበቅ የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ቢሆን የምንፅፋቸው ነገሮች የራሳቸውን የሆነ መልዕክትና ተፅዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡እኛም ሁሌም ልንማር፣ ልናውቅ ፣ ልንጠይቅ እራሳችንን የተሻለ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል፡፡

ከማጠቃለሌ በፊተ ስለታክሲ ጥቅሶች ማውራታችን ካልቀረ እስቲ የታዘብካቸውንና ያነበብኳቸውንና ትንሽ ፈገግ ያደርጋሉ ያልኳቸውን ላካፍላችሁ፡፡

·    የታክሲ ከሌለህ ወርደህ በባስ ሂድ·  ሠውን ማመን ተፈራርሞ ነው·  ፍቅር ካለ ባጃጅ ባስ ይሆናል
·
   በቴሌቶን ሂሳብ መክፈል ክልክል ነው
·
   ሒሳብ ሳይከፍሉ ሀሳብ አይጀምሩ
·
   ለፀባይኛ ተሳፋሪ የፀባይ ዋንጫ እንሸላማለን
·   ለስራ ነው የወጣነው
·   በመጀመሪያ የጋለ ደምህን ተቆጣጠርና ሀሳብህን ግለፅ
·
    ባለጌና ዋንጫ ከወደአፉ ይሠፋል
·
   ኤች.አይ.ቪንና የጫማ ሽታን በጋራ እንከላከል
· 
 ማንችስተር ያሸንፋል አርሠናል ለዘለዓለም ይኑር
·   ሠው አካውንት ይከፍታል አንዳንዱ አፉን ይከፍታል
·   ሞባይል ለጣለ ሲም እንመልሳለን
·   ሹፌሩን መጥበስ ክልክል ነው በነገር
·  ሠው ብቻ ነው የምንጭነው በስህተት የገባ ይውረድ
·  ታክሲ ለሚጠቀሙ ብቻ 
·  ክቡራን ተሳፋሪዎቻችን በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ አስተያየት፣ቅሬታ፣ትዝብት ወይም መሻሻል አለበት የምትሉት ነገር ካለ     አንቀበልም!! መውረድ ይቻላል::
·  ለሠው ቅን ሁን እንጂ ቅንቅን አትሁን
·  ማስቲካ የሚታደል መስሎአችሁ አፋችሁን እንዳትከፍቱ
·  መስኮቱን በመክፈት ለትራፊክ ፖሊስ አያጋፍጡን!
·  ጤነኛ ካልሆኑ መውረጃዎ ደርሷል
·  በጭነት መኪና መታችሁ እዚህ ትቀናጣላችሁ
·  የክፍለ ከተማ ሠዎች ካላችሁ ሒሳብ በቅድሚያ
·  ኑሮአችሁ ሳይሞላ "ታክሲው አልሞላም?! " ትላላችሁ!·  ጥብቅ ማሳሰቢያ ለክቡራን ሌቦች ሒሳብ ሰብስበን ሳንጨርስ ስራችሁን 
መጀመር አትችሉም! የማይስማማ ሌባ ካለ መውረድ ይችላል፡፡
·  ለዓለም ሙቀት መጨመር መንስዔው ጭቅጭቅ ነው
·  ይህ ታፔላ የሚሉት ከመጣ ፤ ምሳችን በቆሎ ራታችን ቂጣ
·  ታክሲው ሳይቆም መውረድ ይቻላል፡፡
·   እንዴት ጭት አትቃሙ ይባላል፣ ሰርቶ የማይዝናና አህያ ብቻ ነው
·  የበታችነት ከተሰማህ ዛፍ ላይ ውጣ
·  ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ ማስፈራሪያ አይደለም
·  የቤትህን አመል እዛው!!!
·  የሠው ትርፍ የለውም . . . ተጠጋጉ!
·  በታክሲ. . . . .  ህግ አላውቅም
·  ታክሲና መንግስተ ሰማያት ሞልቶ አያውቅም
·  ለታላቅ መልስ አይሰጥም
·  ነገን ለመኖር መጀመሪያ ዛሬን ኑር..በመቃም
·  ‹‹ደሀ›› ከፍ ብሎ የሚታየው ባስ ላይ እና እራሱን ሲሰቅል ብቻ ነው፡፡
·  እባክዎን የአባይ ቃል ስላለብን ጠጋ ጠጋ ይበሉልን
·  ለካፌና ለላዳ ብዙ ይከፍላሉ፤ እኛ ጋ ሲሳፈሩ ለምን ይጨቃጨቃሉ
በመጨረሻ
ተሳፋሪ፡- የሰጠከኝ ልክ አይደለም፤ሒሳብ አትችልም
" ? አልተማርክምደደብ . . . .
ወያላ፡- ጋሼ  ድንጋይ ለመጫን እስከ ሁለተኛ ክፍል መማር በቂ ነው

አበቃሁ፡፡

አምሳሉ፤ እንኳን ትሞት ትታመምም አይመስለኝ ነበር

 
ጌታቸው ኃይሌ
ኮሌጅቪል፤ ታኅሣሥ 12 ቀን፤ 2006 (12/21/2013)
ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉና እኔ አብሮ- አደግ አብሮ- ጎልመስ፥ አብሮ -አረግ ነን። 1947 . . የእንግሊዝ ፊደል አብረን ከቆጠርንበት ጊዜ አንሥቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አንድ ዓይነት ትምህርት ለማስተማር እስከተቀጠርንበት ጊዜ ድረስ በቦታ እንኳን ሳንለያይ አብረን ነበርን። በዚህ አምላክ በመረቀልን ረጅም ጊዜ አንድ ቀንም አንዳችን ሌላውን ቅር የሚያሰኝ ቃል ከአፋችን መውጣቱ ትዝ አይለኝም። የተለያየ ጠባይ ያላቸው ሰዎች መፋቀር፥ መተሳሰብ፥ መረዳዳት፥ እንደሚችሉ የአምሳሉና የእኔ ወዳጅነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ለጻፍኩት የሕይወት ታሪኬ ርእሱን የአምሳሉና የጌታቸው ታርክ ብለው የተገባ መሆኑን ያነበበው ሁሉ ሊገምት ይችላል። ረጅሙን በወንድማማችነት አብሮ የመኖር ሕይወታችንን ለማስቀረት ደርግና ሞት ሸመቁበት።

አምሳሉን በዚህ ረጅም ዘመን እንደማውቀው፥ ሞት ቀርቶ ሕመም ይደፍረዋል ብየ አልገመትኩም፤ እሱም አይገምትም ነበር። ሙሉ ጤነኛ ነበር፤ እኔ ሐኪም ቤት ስመላለስ፥ እሱ ሐኪም ቤቱን የሚያውቀው እንደኔ ያሉ ሕመምተኞችን ለመጠየቅ ሲሄድ ነበር። አምሳሉ ጤነኛ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ በተግባር የተመላ ነበር። ሥራ ሲወጥን፥ ሥራ  ሲያጣድፍ፥ ሥራ ሲፈጽም፥ እንቅልፍ አልነበረውም። ሲጫወት፥ ሲያጫውት ሁሉን ያስደስት ነበረ። በዚህ ሁሉ ምክንያት መቶ ዓመት ሳይሞላው ሊሞት ቀርቶ "ሆዴን ጎረበጠኝ" የሚል እንኳን አይመስለኝም ነበር። ግን በኢሳይያስ አፍ፥ "እስመ፡ ኢኮነ፡ ምክርየ፡ ከመ፡ ምክርክሙ፤ ወኢኮነ፡ ፍኖትየ፡ ከመ፡ ፍኖትክሙ።" (ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ አይደለም፤ መንገዴም እንደመንገዳችሁ አይደለም።) የሚለው አምላክ ወንድሜን አምሳሉን፥ እሱ ባሰበው፥ እኛ ባላሰብንበት ዕለት ወሰደው። ሳንሰነባበት ተለያየን። ጽሎቴ ዕለተ ዕረፍቱን የመረጠለት አምላክ ለነፍሱ ከወዳጆቹ ማህል የተደላደለ ቦታ እንዲመርጥላት ነው።
አምሳሉ ሥራ የሚፈጸምለት ታታሪ ሠራተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ብልህና አስተዋይ በመሆኑ ጭምር ነው። በብልህነቱ፥ በዐዋቂነቱ እቀናበት እንደነበረ ከእሱ በቀር ማንም አያውቅም። ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ማንም ሳያያቸው እሱ ቀድሞ ያያቸዋል። አምሳሉ በዘመኑ ሥልጣኔ በተራመዱት አገሮች በአንዱ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ፥ በሀብትም ሆነ በሙያ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ታዋቂዎች አንዱ ይሆን ነበር። ሲዘፍን፥ ቲያትር ሲሠራ፥ ያፈዝ ነበረ።
አምሳሉ ቀለመወርቅን በማግኘቱ ዕድለኛ የኖነውን ያህል እሷም አምሳሉን የመሰለ አጫዋችና አፍቃሪ የሕይወት ጓደኛ በማግኘቷ ዕድለኛ ነች። በአካል ቢለያዩም ትዝታውንና ጨዋታውን እያስታወሰች እንዳዲስ ስትስቅ እንደምትኖር እርግጠኛ ነኝ።  
አምሳሉ ቀለመወርቅን ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ሲል እኔም ትንሽ ሚና ተጫውቻለሁ፤ ከመልካም ቤተሰብ የተወለደችና ጎልማሳ የምታፈዝ ቆንጆ ልጃገረድ ስለነበረች ለትዳር የሚመኟትና የሚፈልጓት ጥቂቶች አልነበሩም። አንዱ በተለየ ጓደኞቹን አስሰልፎ  ሊያስፈራራ ሲመጣ "አጭር ብትፈልግ አጭር፥ ረጅም ብትፈልግ ረጅም ሆነን መጥተንብሃልና የምትፈልገውን አሳየንና እናሳይ አልነው። ማን እንዳሸነፈ የአምሳሉና የቀለመወርው ልጆች ምስክር ናቸው።
እኔም እንደቀለመወርቅ በጨዋታው ሳስታውሰው እኖራለሁ። በትምህርት ገበታ ላይ ብቻ ሳይሆን አገር ለመጎብኘትም አብረን ብዙ ነገር አይተናል። ኪሳችን የተማሪ ኪስ ስለነበረ፥ አገር የምናየው መንገድ ላይ እየቆምን ባለመኪና ሲመጣ እየለመንን ነበር። የለማኝ መራጭ ስለሌለው፥ የቆመልን ሁሉ ይወስደናል። አንዳንድ ጊዜ ባለመኪናዎቹ ሁለት ሰው ስለማይወስዱ አውላላ ሜዳ ላይ እንለያያለን። ቀጠሯችን ባቡር ጣቢያ ነው። አንድ ቀን ባቡር ጣቢያ ስንገናኝ፥ "አምሳሉ፤ የዛሬው ጉዞህ እንዴት ነበር?" አልኩት።
"እረ እባክህ ተወኝ" አለ። "ምነው?" ብለው፥ "አንዲት ሴትዮ በዶቅዶቂት አሳፈረችኝ" አለኝ። "ታዲያ ምኑ ነው፥ እረ እባክህ ተወኝ የሚያሰኘው?" ብለው። "እንዳልወድቅ ትከሻዋን ነበር የያዝኩት፤ እንደሱ አይደለም፤ ወገቤን ያዝ" አለችኝ። ልንሄድበት ስንደርስ ልቀቀኝ ባትለኝ እዚያው ተጣብቄ ልቀር ነበር" አለኝ።
አይ አምሳሉ፤ ለካ አንተም እንደሌላው ነህ!! ግን የምንጽናናባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። በጤና ኖረሃል። መልካም ባለቤት፥ መልካም አባት፥ ታማኝ ወዳጅ ሆነሃል። የልጅ ልጅ ስመሃል። በዕውቀትህ የአገርህን ልጆች አገልግለሃል። ለስምህ ሐውልት ተክለሃል። የፈለከውን ለማድረግ አምላክ ዕድል ሰጥቶሃል። ክብሩ ይስፋ። ለዘላለሙ ሕይወት በሚኬድበት መንገድ የሄድከው የማይቀር ቢሆን ነው። ቤተሰብህን፥ ዘመዶችህን፥ ወዳጆችህን እግዚአብሔር ያጽናቸው። እንደኔ ምስጢረኛ አያሳጣቸው።
ምንጊዜም የማይረሳህ ወንድምህ
ጌታቸው ኃይሌ

ሟሙቷል:

ሟሙቷል

 አለልኝ መሀመድ ሰሞኑን ነዉ፡፡ ከስራ ወጥቼ ቤቴ ስደርስ፤ ድብርብር አለኝ፡፡ ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ የምወዳት ልጅ ቀጥራኝ ስለቀረች ግን አይደለም፡፡ በእርግጥ ሰዉ ቀጥሮኝ ሲቀር ይደብረኛል፡፡ ነገር ግን ቀጥራኝ የምትቀር አይነት ሴት አላፈቅርም… ሲጀመር፡፡ ስለዚህ የድብረቴ ምክንያት ሌላ ነዉ፡፡፡
ለማንኛዉም፤ ከድብርት ለመላቀቅ ቤቴን ጥየ ወጣሁ፡፡ ከቤቴ ብዙም ሳይርቅ ደግሞ አንድት አነስ ያለች፤ ጫጫታ የማይበዛባት ካፌ አለች፡፡ የሄድኩት ወደ እዚች ካፌ ነበር፡፡ ስገባ ታድያ በሩ አካባቢ፤ በግምት፤ እዚች ምድር ላይ ለ47 አመታት ያህል የተሰቃየ የሚመስል አንድ ጎልማሳ፤ የነተበ ነጭ ሸሚዝ በቡኒ ጃኬት ለብሶ፤ በትልቅ ብርጭቆ የቀረበለትን ሻይ፤ በትንሽ ማንኪያ ያማስላል፡፡
ከሰዉየዉ ብዙም ሳልርቅ ፊት ለፊቱ ያለዉ ወንበር ላይ ተቀመጥኩ፡፡ የካፌዋ አስተናጋጆች መግባቴን አይተዉ እስከሚታዘዙኝ ድረስ፤ ሰዉየዉን ማየት ጀመርኩ፡፡
ሰዉየዉ ረጋ ብሎ ሻዩን እያማሰለ፤ አይኑን በመስታወቱ አሳልፎ ዉጭዉን አሻግሮ ያያል፡፡ እኔም የማያገባኝን የዚህን ሰዉየ ሁኔታ ተመስጨ በመከታተል ላይ እያለሁ፤ አንዲት ቀጫጫ አስተናጋጅ ወደኔ መጣች፡፡
“ምን ልታዘዝ?”
“ማኪያቶ!” … አልኳት፡፡
“ነጣ ያለ ይሁንልህ ወይስ ጠቆር ያለ?”
“ይቅርታ ሻይ ማለቴ ነዉ፡፡ ማኪያቶዉን ተይዉ፡፡” … አልኳት፡፡
እሽ… ስትለኝ…”እንደዉም ማኪያቶ ይሁንልኝ በቃ፡፡ ሻዩን ተይዉ፡፡” አልኳት፡፡
ወዲያዉ ደግሞ …”ግን ሻይ ይሻለኛል መሰለኝ …” ስላት ተናዳ ይመስለኛል፤ ፊቷ ኮስተር ማለት ሲጀምር “ይቅርታ ተመልሰሽ ትመጪ እናትይ” አልኳት፡፡ (‘አስቤ ልንገርሽ’ ነገር ነዉ ሁኔታየ፡፡)
ልጅቷ ስትሄድ፤ ከሻይ እና ከማኪያቶ አንዱን መምረጥ ለምን እንደከበደኝ ማሰብ ጀምርኩ፡፡ ሲገባኝ ታድያ፤ ለካ ነገሩ እንዲህ ነዉ… መጠጣት የፈለኩት ማኪያቶ ነዉ፡፡ መጠጣት የምችለዉ ግን ሻይ ነዉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀን ላይ፤ ከምሳ በኋላ አንድ ማኪያቶ መጠጣቴ ነዉ፡፡ በቀን ሁለት ማኪያቶ የሚያስጠጣ አቅም እንደሌለኝ፤ እንኳን እኔ ማንም ያዉቃል፡፡
እንደዉም አንድ ኢኮኖሚስት ጓደኛየ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ‘በኢኮኖሚክስኛ’ ‹‹በጀት ኮንስትሬይንት›› ተብሎ እንደሚጠራ ነግሮኛል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለዉ፡፡ ያማረኝን ማኪያቶ ካላስጠጣኝ ቃሉ ምን ይጠቅመኛል…??? ስለዚህ ኢኮኖሚስቶቻችን እባካችሁ ቃሉን እና ትርጉሙን ከምትነግሩን፤ መንስኤዉንና መፍትሄዉን ንገሩን፡፡
ለማነኛዉም ችግሩ ‹‹በጀት ኮንስትሬይንት›› መሆኑ ሲገባኝ ልጅቷን ጠርቼ ያለምንም ማቅማማት ሻየን አዘዝኩኝና ሀሳቤን ሻይ ወደ ሚያማስለዉ ሰዉየ መለስኩት፡፡ ሰዉየዉ አሁንም ሻዩን ያማስላል፡፡ ሻዩን ግን አያየዉም፡፡
ያዘዝኩት ሻይ መጣና አይኔን ከሰዉየዉ ላይ ሳልነቅል ሻየን አማስየ ጠጣሁ፡፡ ሰዉየዉ ግን አሁንም ያማስላል፡፡ ሁኔታዉ ግራ ስለገባኝ አንገቴን አርዝሜ ሻዩ ዉስጥ ያለዉን ነገር ለማየት ሞከርኩ፡፡ ምንም የለም፡፡ ስኳሩም ሟሙቷል፡፡
እናም አላስችልህ ስላለኝ… ሰዉየዉን በእጄ ጠርቸ… “ይቅርታ ወንድም ሟሙቶልሀል፡፡” አልኩት፡፡ “ምኑ?” አለኝ፡፡ “ስኳሩ” አልኩት፡፡ “የምን ስኳር?…” ሲለኝ…”ማለት… ሻይ እያማሰልክ አይደል? ስኳሩ ማሙቷል ነዉ የምልህ፡፡ እንዳይቀዘቅዝብህ ብየ ነዉ::”… አልኩት ሻዩን በእጄ እየጠቆምኩ፡፡ ሰዉየዉም… “እ…እ…እ .. እሺ” አለና በሁኔታዉ እንደማፈር ብሎ ሻዩን ለመጀመሪያ ጊዜ ጐንበስ ብሎ አየዉ፡፡
እኔም፤ ባልጠበኩት ሁኔታ ሰዉየዉ ሲሸማቀቅ ሳየዉ፤ እራሴን ወቀስኩት፡፡ እናም.. “እስቲ እንደዚህ ከማሳቅቀዉ፤ መናለ ዝም ባልኩት ኖሮ…? ለዛዉም ለቀዘቀዘ ሻይ … ወይ መጀመሪያ አልነገረኩት… ምን አይነት ሰዉ ነኝ?…” እያልኩ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ከካፌዉ ተነስቼ ወጣሁ፡፡ ሰዉየዉንና የሰዉየዉን ሻይ በሀሳቤ ይዤ ትንሽ እንደተራመድኩኝ ግን… “ወንድም … ወንድም…” የሚል ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ዞር ስል የካፌዉ አስተናጋጅ ነች፡፡
“ይቅርታ ሂሳብ…” አለችኝ ፡፡
“የምን ሂሳብ” አልኳት፡፡
“የሻይ ሂሳብ፡፡” ስትለኝ
“የማን ሻይ?” አልኳት፡፡
እርሷም… “ማለት ሻይ ጠጥተህ የለ? ሂሳብ አልሰጠኸኝም…” ስትለኝ …የጠጣሁት ሻይ ትዝ አለኝና “እ…እ…እ… እሺ፡፡ ስንት ነዉ?” ስላት…”አምስት ብር ከ ሰባ ሳንቲም አለችኝ”. . . ዘና ብላ፡፡ (እኔ እርሷን ብሆን ሂሳቡን ለመናገር እሳቀቅ ነበር::)
እናም፤ ብሩን ከፍየ፤ ድብርቴም ከበፊቱ ብሶ ወደ ቤቴ ተመለስኩ እላችኋለሁ፡፡ ግን ጭንቅላቴ ዉስጥ ሲመላለስ የነበረዉን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ምናልባት የናንተም ጥያቄ ከሆነ፡፡
****
እኔን፤ ማኪያቶ መጠጣት እየፈለኩ፤ ሻይ ያስጠጣኝ…፤ ሰዉየዉን ከ አምስት ደቂቃ በላይ ሻይ እንዲያማስል ያደረገዉ…፤ በስተመጨረሻም እኔና ሰዉየዉ እንድንሸማቀቅ ያደረገን…፤ እንዲሁም አስተናጋጇን ሂሳብ ለመቀበል ዉጭ ድረስ እንድትሄድ ያደረጋት…ምክንያቱ ምን ይሆን?
የኑሮ ዉድነቱ ይሆን?