Jul 28, 2012
ፈረንጅ ነውኮ ( በ ዲ/ንዳንኤል ክብረት)
ፈረንጅ ነውኮ
ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓም የተዘጋውን የኢንተርኔት መሥመር ለማስከፈት እዚህ አያት መንገድ ጉርድ ሾላ ያለው የቴሌኮሙኒኬሽን ቅርንጫፍ ሄድኩላችሁ፡፡ በጠዋቱ ሠልፉ ለጉድ ነው፡፡ ምናለ የቀበሌ መስተዳድሮች ለአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥልጠና ቢሰጡ? ቀበሌ እንኳን የጠፋው ሰልፍ እዚህ ከነ ሙሉ ክብሩ ይንጎማለላል፡፡ አዛውንትና አሮጊቶች እግራቸው እየተንቀጠቀጠ ውጭ በብርድ ቆመዋል፡፡ ያውም ከሠላሳ ደቂቃ በላይ፡፡
እንደምንም ተራ ደርሶኝ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያም ለካስ ሌላ ሰልፍ አለ፡፡ ደግነቱ እዚህ የምትሰ ለፉት ተቀምጣችሁ ነው፡፡ ፊት ለፊታችን የተገተሩት ኮምፒውተሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ሰዎች ግን ሦስት ኮምፒውተር ለአንድ ሠተራኛ እንዲደርሳቸው ሆነው ነው፡፡ አሁን እነዚህ ሁሉ ኮምፒውተሮች የሚሠራባቸው ከሌለ ለምን ተገዙ? ከተገዙስ ለምን አይሠሩም? ማን መልስ ይሰጣችኋል? ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ አለ ያገሬ ሰው፡፡
እኛ ካሁን ካሁን ደረሰን እያልን ማርያም ማርያም ስንል አንድ ሕንድ ቦርሳውን አንጠልጥሎ መጣ፡፡ የሚያስተናግዱን ሴትዮ ቀጥ አድርገው ወደ መስተንግዶው ወንበር ወሰዱት፡፡ ይታያችሁ ውጭ አያሌ አዛውንትና አሮጊቶች ቆመዋል፡፡ ውስጥ እኛ ተቀምጠናል፡፡ አላስቻለኝምና ሰውዬውን ተራ እንዲይዝ በሚያውቀው ቋንቋ ነገርኩት፡፡ ወዲያው አስተ ናጋጇ «ተወው» አሉኝ፡፡ ገርሞኝ ወደ እርሳቸው ሄድኩና «ለምን?» ስል ጠየቅኳቸው፡፡ «ፈረንጅኮ ነው» ብለውኝ እርፍ፡፡
ይሄኔ አዝኜም ተናድጄም «እና ፈረንጅ ቢሆንስ፤ ፈረንጅ አይሰለፍም? ተራ አይጠብቅም? መመሪያችሁ ያዝዛል?» ደረደርኩት ጥያቄዬን፡፡ ምንም አልመሰላቸውም፡፡ «አንድ ሰው ነው ቢገባ ምናለ» አሉኝ «እዚህኮ በቡድን የመጣ የለም፡፡ ሁላችንም አንዳንድ ሰዎች ነን፡፡ እንደዚህ ለሰው ካሰባችሁ ለምን እዚያ ወገባቸው የሚንቀጠቀጠውን አሮጊቶችና አዛውንት አታስቀድሟቸውም» አልኳቸው፡፡ «እነርሱማ የኛው ናቸው እርሱ ግን ፈረንጅ ነው»
ይኛን ጭቅጭቅ ሰምተው የቦታው ኃላፊ ይመስሉኛል ሌላ ሴትዮ መጡ፡፡ «ምን ሆናችሁ ነው?» አሉን፡፡ ነገርኳቸው፡፡ «አይዞህ ይደርስሃል፤ አትጨቃጨቅ፡፡ ምናለ አንድ ሰው ነው፡፡» ማለሳለሳቸው ነው፡፡ ሌላም ሰውዬ «አንድ ሰው ነው ማለት ምን ማለት ነው? እኛስ ስንት ሰው ነን?» ሲል ሁላ ችንም ሳቅን፡፡ ሌላ ተስተናጋጅም «ቅድም እኒያ አሮጊት በምርኩዝ መጥተው አላስገባም አላላችሁም? እኛ አይደለን ይግቡ ግዴለም ብለን ያስገባናቸው? እርሳቸው ለሀገራቸው ሠርተዋል፤ ልጆች አሳድገዋል፤ በእድሜም አርጅተዋል፤ ለእርሳቸው ሳታዝኑ እንዴት ለሕንዱ አዘናችሁለት?» ሴትዮዋ ነገሩ መክረሩን ሲያውቁ፡፡
«በቃ ተውት፤ ምናልባት ተራ ያዝ ለማለት ቋንቋውስ ከየት ይመጣል ብላችሁ ነው» ብለው ሁላችንንም አሳቁን፡፡
እኛም «ምናልባት ቴሌ ኮሙኒኬሽን ኢትዮ ቴሌኮም ተብሎ ፈረንጆቹ (ፈረንሳውያን) አስተዳደሩን ስለ ያዙት ለፈረንጅ ቅድሚያ እንዲሰጥ ታዝዞ ይሆናል እያልን ወረፋችንን ይዘን ትንታኔያችንን ቀጠልን፡፡
አንዳንድ ወረፋ ያዦች ብዙ ቦታ ሲሄዱ ፈረንጅ ሲፈተሽ እንደማያዩ ተናገሩ፡፡ ሌሎችም በቤተ ክርስ ቲያን ከፈረንጅ ጋር ለሚጋቡት የተለየ ክብር እንደሚሰጥ፣ ለሌላው የማይደረግ የቀኖና ማስተካከያ እንደ ሚደረግ ያጋጠማቸውን አወጉን፡፡ ሌሎችም በየፋብሪካውና በየግንባታ ኩባንያው በስመ ፈረንጅ የመጡ ነጮች ሠራተኛውን ሲደበድቡና ሲበዘብዙ ፈረንጅ በመሆናቸው ብቻ ሃይ የሚላቸው እንደሌለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአካባቢው ለሚገኙ የመስተዳድር አካላት ሲያመለክቱም ከአበሾቹ ይልቅ ፈረንጆቹን መስማት እንደ ሚመርጡ ይተርኩ ጀመር፡፡
ይሄኔ ነው የኦፕራ ገጠመኝ ትዝ ያለኝ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ታዋቂዋ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር አዘጋጅ ኦፕራ ዊንፍሬ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ያጠማትን ነገር ኀዘን በተሞላበት ሁኔታ የገለጠችበትን ዝግጅት አቅርባ ነበር፡፡ እርሷ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ አራት ጠባቂዎችን ቀጥራ ነበር፡፡ ችግሩ ቀጣሪዋ ኦፕራ ጥቁር፣ ተቀጣሪዎቹ ደግሞ ነጮች ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያ ደርሳ ከአውሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ ኦፕራ ያላገኘችውን ክብርና መስተንግዶ እርሷ የቀጠረቻቸው ነጭ ጠባቂዎቿ እንዴት ያገኙት እንደነበር በኀዘን ገልጣ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት አምባ ትባላለች እንጂ ራስዋን እንደ ጥቁር አፍሪካ አካል አድርጋ አትመለከትም የሚል ትችትም ሠንዝራ ነበር፡፡
አንዲት አፍሪካውያን በሚበዙበት ድርጅት የምትሠራ ወዳጄ አብራት ለምትሠራው አፍሪካዊት እኅቷ የቤት ሠራተኛ ታፈላልግላታለች፡፡ የቤት ሠራተኛዋ የቀጣሪዋን የሥራ ቦታ ስታውቅ ደሞዙን ሞቅ አደረገችው፡፡ ያችም የሰው ሀገር ሰው አማራጭ ስላልነበራት ተስማማች፡፡ ሥራ የምትጀምርበትን ቀን ቆረጠና የኔ ወዳጅ የቤት ሠራተኛዋን ይዛ ወደ ቀጣሪዋ ቤት ሄደች፡፡
እዚያ ስትደርስ የቤት ሠራተኛዋ ሃሳቧን ቀየረች፡፡ «ቤቱ ሩቅ ነው፤ ትልቅ ነው» የሚሉ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያት መደርደር ጀመረች፡፡ ብትባል ብትሠራ አልነካውም አለች፡፡ በነገሩ አዝ ነው ቀጣሪዋና አስቀጣሪዋ ተሰነባበቱና አስቀጣሪዋ ያችን የቤት ሠራተኛ በመኪናዋ ይዛት ወጣች፡፡
መንገድ ላይ «ከተስማማሽ በኋላ ሃሳብሽን እንዴት ትቀይሪያለሽ? ለምን መጀመርያ አልነገርሽኝም ነበር» አለቻት አስቀጣሪዋ፡፡ የቤት ሠራተኛዋም «እኔ ፈረንጅ መስላኝ ነበር እንጂ» ስትል አስቀጣሪዋ በንዴት መኪናዋን አቆመችና «አንቺ ከደመወዝሽና ከሥራው እንጂ ከሴትዮዋ ቅጣትና ጥቁረት ምን አለሽ?» አለቻት፡፡ «እንዴ እኔ ጥቁር ቤት እሠራለሁ ማለት አፍራለሁ» ብላት ዕርፍ፡፡ እንግዲህ እርሷ ነጭ መሆንዋ ነው፡፡
አንዱ ችግራችን ራሳችንን የጥቁር አፍሪካ አካል አድረገን አለማየታችን ይመስለኛል፡፡ ስለሌሎች አፍሪካ ውያን ስናወራ እንኳን «ጥቁሮች» እያልን ነው፡፡ የመንግሥቱ ለማ ባሻ አሸብር እንደሆኑት ማለት ነው፡፡ ጥቁርነታችንን አለመቀበላችን ለነጭ የተለየ ቦታ እንድንሰጥ አድርጎናል፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮ ጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር እየሄድን ለመኖር የተለየ ጉጉት ካደረብን ካለፉት ዐርባና ሠላሳ ዓመታት ወዲህ ከፈረንጅ ጋር መሥራት፣ ፈረንጅ ሀገር መሄድ፣ በፈረንጅ ቋንቋ መናገር፣ የፈረንጅ ልብስ መልበስ፣ የፈረንጅ ምግብ መብላት፣ ፈረንጅ ማግባት፣ ፈረንጅ መቅጠር፣ የፈረንጅ ፊልም ማየት፣ የፈረንጅ ስም ማውጣት፣ ፈረንጅ ማስተናገድ፣ የክብርና የደረጃ ማሳያዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡
ዛሬ ዛሬ ያ በሽታ አድጎ አድጎ ተቋሞቻችንና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ፈረንጅ መቅጠር፣ በፈረንጅ መመራትና አስተዳደሩን ለፈረንጅ መስጠት የሥልጣኔና የደረጃ መሳያ አድርገውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ይቺ በመዳህ ላይ ያለቺው የፊልም ጥበባችን እንኳን በፈረንጅ ቻይናዎች እየተሞላች መጥታለች፡፡ በሙዚቃ ክሊፖቻችንም ፈረንጅ እስክስታ ሲመታና ሞሰብ ከብቦ እንጀራ ሲመገብ ማሳየት የተወዳጅነቱ ማሳያ ሆኗል፡፡
ስለ አድዋና ማይጨው፣ ስለ ሦስት ሺ ዘመን ነጻነትና ስለ ቅኝ አለመገዛት የምናወራው ሁሉ እንደ ላሜ ቦራ ተረት እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶች እንኳን ሲፎካከሩ «እዚህ ቤት ነጮች ብቻ ናቸው የሚያዘወትሩት» መባልን የክብራቸው መለኪያ ሲያደርጉት ታያላችሁ፤ ትሰማላችሁም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተ እምነቶቻችን እንኳን ለሀገሬው ሰዎች አይነኩም አይዳሰሱም የሚባሉትን ነገሮች ለፈረንጆች መፍቀድና ማሳየት ነውር አይመስላቸውም፡፡
ይሄው ለነጮች አልገዛም ብሎ የኖረው መሬት እንኳን ዛሬ ነጭ በነጭ እየሆነ አይደለ፡፡ መሬት ወሰዱ ሲባል የምሰማቸው ሁሉ «ፈረንጆቹ» ናቸው፡፡ መሬት ወሳጆቹም ነጮች፣የሚዘራውም ነጭ፣ የሚሸ ጠውም ለነጭ፡፡
እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይ በምዕራብ ሀገሮች ቆይተው የሚመጡ ዳያስጶራ ኢትዮ ጵያውያን ከፈረንጅ ጋር መኖር ያረንጅ ይመስል ራሳቸውን እንደ ፈረንጅ መቁጠራቸው ነው፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤት ስትሄዱ፣ ወይም አንዳንድ ጉዳይ የሚፈጸምባቸው ቢሮዎች ስትገቡ ዳያስጶራ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዴማ እነርሱ ከውጭ ስለሚመጡ ብቻ የሊዝ ዋጋ ለእነርሱ እንዲቀንስ፣ መሬት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፤ መኪናና የቤት ዕቃ ያለ ቀረጥ እንዲ ያስገቡ፣ በየቢሮው የተለየ አስተያየት እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ባለፈው እንኳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፋሲካ ሰሞን ሰብስቧቸው ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳችም ነገር ሳያነሡ ለዲያስጶራ ይሄ ይደረግለት፣ ይሄ ይፈቀድለት፣ ይሄ ይሟላለት እያሉ ሲጠይቁ ነው የዋሉት፡፡ ፈረንጆች፡፡
እነርሱ ምን ያድርጉ በኢትዮጵያ ፓስፖርት ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የማይፈቀደው ላፕቶፕ እንኳን በውጭ ሀገር ፓስፖርት ለሚገቡ «ኢትዮጵያውያን» ሲፈቀድ ያያሉ፡፡ አበሻ ከመሆን ይልቅ ፈረንጅ መሆን ሲያስከብር አይተዋል፡፡ ታድያ ቢፈረንጁ ምን ይገርማል፡፡Jun 27, 2012
Jun 23, 2012
በአቤ ቶኪቸው
አቤቱታ! የፀሎት፣ የቁዘማ እና የህልም ማጭበርበር አዋጆች እንዲወጡ ስለመጠየቅ፤ (አቤ ቶኪቻው)
(ይቺ ጨዋታ በትላንቱ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ወጥታ ነበር! ታድያ የብሎጋችን ታዳሚያንስ ለምን አያነቡልኝም… እባክዎ ተቸገሩልኝ ወዳጄ…!)
ውድ የፍትህ ጋዜጣ ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ? ከዛሬ ነገ ብቅ እላለሁ እያልኩ ሳይሳካልኝ እየቀረ ተጠፋፍተን
ከረምን እኮ! ፌስ ቡክ ሰፈር ግን በብዛት አለሁ። በየ ዕለቱ የሆነ ነገር ሳልል የዋልኩበት ጊዜ የለም። እንደውም
ባለፈው ጊዜ “ኑ ፌስ ቡክ ሰፈር እንሰባሰብ” የሚል አንድ ጨዋታ ለእርስዎ ብዬ አዘጋጅቼ፤ ለአርብ ሳይደርስልኝ
ቀረና ብሎጌ ላይ ለጥፌው ነበር። የፍትህ አዘጋጆች ከፈቀዱልንና ጨዋታው አዲሳባ ሌላ የህትመት ሚዲያ ላይ ያልወጣ
ከሆነ እሱን ጨዋታ በሚቀጥለው ጊዜ እንቃመሰው ይሆናል።
ወደ ዛሬው ጨዋታችን ስንመጣ ለመንግስቴ አንድ አቤቱታ ማቅረብ ፈልጊያለሁ… እስቲ አብረን አቤት እንበል፤
እኔ አመልካቹ ግለሰብ ሀገራቸን በየጊዜው የምታወጣቸው አዎጆችን በደስታ የምመለከታቸው ሲሆን ለእያንዳንዱ አዋጅ ደግስ ደግሼ ዘመድ ጎረቤት ጠርቼ በደስታ እና በሀሴት ሳሳልፍ የኖርኩ ትጉህ ነኝ።
በአሁኑ ግዜ ሀገራችን በርካታ አዋጆችን እያወጀች እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ታላቅ የአዋጅ
እመርታ አሳይታለች። ይህም ለቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እና ለሰላማችን የሚኖረው አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልሆነ እሙን
ነው። እንዲሁም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መፋጠን፣ ድህነትን ለማጥፋት እና ለመሳሰሉት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች፤
አዋጆች በየጊዜው መታወጃቸው በእውነቱ አስደሳች ነው።
አሁን በቅርቡ የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ማጭበርበር አዋጅ ታውጇል። አዋጁን እንዳየሁት፤ ላካስ እስከዛሬ ስንጭበረበር ኖረናል! መንግስታችን ባይደርስልን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር!? ብዬ በእጅጉ አመስግኛለሁ።
ይህ የቴሌኮም ማጭበርበር፤ “ከኢኮኖሚያዊ ኪሣራ ባሻገር የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሆኗል”
መባሉን ስሰማማ እስከዛሬ በሰላም መቆየታችን በእውኑ ከመንግስታችን የተነሳ ነው ስል አጥብቄ አመስግኛለሁ።
በተለይም በአዋጁ ውስጥ፤ “በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር የተያያዘ ሽብር የሚያስከትል መልዕክት
ለማሰራጨት፣ ወይም በወንጀል ህግ የሚያስቀጣ አስነዋሪ መልዕክቶችን ለማሰራጨት በማንኛውም የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያና
ኔትወርክ መጠቀም እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ 80 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት
ያስቀጣል፡፡” የሚለውን ስመለከትማ የመንግስቴ ጥንቃቄ እና ዕቅድ ወለል ብሎ ታየኝ እና በደስታ ጮቤ ረገጥኩ።
በእውነቱ ከሆነ ይህው ጉዳይ እኔ አመልካቹንም በጣም ሲያሳስበኝ የከረመ ጉዳይ ነው። በተለይም ከአረቡ ሀገራት
አብዮት በኋላ ልጅ ከአዋቂ ሳይለይ በየ ኢንተርኔቱ እተንጠለጠለ፣ መንግስቴን እያብጠለጠለ እና ጥሪውን እያቀጣጠለ
በየቦታው “ለነፃነት ለፍትህ ተነሱ” እያሉ የሚተኩሱ የፌስ ቡክ ሸማቂዎች ተበረክታው በተመለከትኩ ጊዜ ይህንን
ማዕበል በምን እንቀቋቋመው ይሆን? ስል አብዝቼ ሳስብ ከርሜያለሁ።
በእውነቱ እኛ በየቀበሌው ወጣቶችን
በአነስተኛና ጥቃቅን ስናደራጅ አነዚሁ ወጣቶች ከሌሎች ጋር በመቀናጀት፤ በኮምፒውተር እና በሞባይላቸው በኩል
በትላልቅ እና ከፍተኛ ሁኔታ ራሳቸውን ለአመፅ እና እምቢ ባይነት እያደራጁ እንደሆነ ስጠረጥር ከርሜያለሁ።
“ያልጠረጠረ ተመነጠረ!” ያሉት ቤን አሊ ናቸው ወይስ ሙባረክ…? ጋዳፊ ይሆኑ እንዴ… ብቻ! እንጃ ያልጠረጠረ
ተመነጠረ ነው ነገሩ።
ነገር ግን ጠርጣራው መንግስታችን ቀድሞ በወሰደው አዋጅ የማውጣት እርምጃ
በርካቶች በፌስ ቡክ እና በመሳሰሉት የኢንተርኔት ሰፈሮች ሲያጧጡፉት የነበረውን በሽብርተንነት አዋጁ የሚያስቀጣ
አመፅ ቀስቃሽ የመረጃ ልውውጦች፤ ባይገታውም ማንኛውም የፌስ ቡክ አርበኛ በከባድ ጥንቃቄ እና ስጋት ውስጥ እንዲገባ
አደርጎታልና አዋጁ ምስጋና ይገባዋል።
ታድያ ይህ አዋጅ የተሟላ ይሆን ዘንድ ከላይ በርዕሱ የተገለፁትን የማጭበርበር አደጋዎች የሚገታ ሌላ አዋጅ ቢወጣበት መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።፡
አንድ፤ የፀሎት ማጭበርበር አዋጅ
በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ በየ ቤተ ክርስቲያኑ እና በየ ቤተ መስጊዱ በሚሄድበት ጊዜ በፀሎቱ ምን እያለ እንደሚፀልይ
መገመት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እንደኔ እምነት ይሄም በሀገሪቱ ላይ ታላቅ የደህንነት ስጋት ነው ብዬ
አምናለሁ።
ምዕመኑ በየ እምነት ቦታው “በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር የተያያዘ
ሽብር የሚያስከትል ፀሎት እየፀለየ እንደሆነ በምን ይታወቃል!? በእውኑ በየእምነት ተቋማቱ መንግስታችን ላይ ጉዳት
እንዲደርስ ወይም ከመንበሩ እንዲነቃነቅ ወይም እንዲፈናጠር አምላክን የሚለማመኑ ግለሰቦች መበራከታቸው እኔ አመልከቹ
መረጃ አለኝ፤ ይህም ፀሎትን ላለተፈለገ አላማ ማዋል ነው። ስለሆነም ወንጀሉ “ትልቅ በፀሎት የማጭበርበር ወንጀል”
መሆኑ እንዲታወቅ እጠይቃለሁ።
ይህንን ለመከላከልም በፀሎት ማጭበርበርን የሚገታ አዲስ አዋጅ
እንዲወጣ አቤት እላለሁ። በአዋጁ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በፀሎታ የማጭበርበር ወንጀል ለመፈፀሙ ወይም
ሊፈፅም ለመሆኑ ፖሊስ ካመነ በድብቅ በሚደረግ የብርበራ ማዘዣ ፈቃድ ከፍርድ ቤት አውጥቶ አዕምሮውን እንዲበረብር
ስልጣን እንዲሰጥም አመለክታለሁ።
ሁለት፤ የቁዘማ ማጭበርበር አዋጅ
መንግስታችን
ከእንግዲህ ወዲያ በከተማው ውስጥ ኮምፒውተርን ወይም ስልክን በመጠቀም በ”ስካይፒ” ወይም በሌሎች መሰል ቴክኖሎጂዎች
እየተደዋወሉ ከልብ ወዳጅ ጋር የሚደረግን ግንኙነት በአዋጅ መከልከሉ ይበል የሚያሰኘው ነው። ምክንያቱም ከላይ
እንደተገለፀው በኢኮኖሚ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በተጠቀሱት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የሚደረግ ግንኙነት ሰዎቹ
ምን እየተባባሉ እንደሆነ ለማወቅ የማይቻል በመሆኑ፤ የሀገር ደህንነት ስጋትም እንደሚሆን በመታመኑ ነው።
ታድያ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቦቹ ከልብ ወዳጃቸው ጋር የሚያደርጉት ድብቅ ውይይት እንደመከልከሉ ከራሳቸው ልብ
ጋር የሚያደርጉት ውይይት ወይም ቁዘማ ለመጥፎ አላማ ሊያውሉት ይችላሉ ብሎ አመልካቹ ያምናል። ይህም ቁዘማን
ላልታሰበለት አላማ በማዋል የቁዘማ ማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ያስችላል። ይህ በቸልታ ከታየ የሀገሪቱ
ደህንነት ስጋት መሆኑ አያጠራጥርም።
ለመሆኑ በዚች የጥጋብ እና የተድላ ሀገር ላይ አንድ ግለሰብ
በመንግስት ላይ እያሴረ ካልሆነ በስተቀረ የሚቆዝምበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? በመንግስት ላይ ማሴር ደግሞ
በሽብርተኝነት አዋጁ የተከለከለ ነው።
ስለዚህም አንድ ግለሰብ በመንገድ ላይ፣ ወይም በቤቱ፣ ወይም
በመስሪያ ቤቱ፣ ወይም በሁሉም ቦታ ከራሱ ጋር ሲወያይ ወይም ቁዘማ ሲያደርግ የተገኘ እንደሆነ ልክ በስካይፕ ወይም
በሌላ ቴክኖሎጂ ከልብ ወዳጅ ጋር በድብቅ ሲወያይ እንደሚቀጣው ከሶስት እስከ ስምንት አመት ፅኑ እስራት እና እስከ
ብር ሰማኒያ ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት እንዲጣልበት የመቆዘሚያ መሳሪያዎቹም በመንግስት እንዲወረሱበት የሚደነግግ
አዋጅ እንዲወጣ እጠይቃለሁ።
ሶስት፤ የህልም ማጭበርበር አዋጅ
በአዲሱ የቴሌ ኮም
ማጭበርበር አዋጅ ውስጥ “አለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን የአገር ውስጥ በማስመሰል (ኮልባክ) ወንጀል በየዓመቱ
በበርካታ ሚሊዮን የሚገመት የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ እንድታጣ እያደረጋት” እንደሆነ ተጠቁሞ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ
ግለሰቦች እስከ አስር አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲበይንባቸው ያዛል። ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ…!
እኔ አመልካቹ ግለሰብ ደግሞ የህልም ማጭበርበር ከዚህም የከፋ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን የሚያሳጣ እንደሆነ
ደርሼበታለሁ። ይህ በህልም ማጭበርበር ወንጀል ሰዎች በቴሌኮም ማጭበርበር አዋጁ የተከለከሉትን በሙሉ “እንደ ቪዲዮ
ኮል” እና “አለም አቀፍ ህልሞችን የሀገር ውስጥ አስመስሎ እንደማየት” የመሳሰሉትን ግንኙነቶች በቴሌ በኩል ብቻ
ማድረግ ሲገባቸው በህልማቸው እንደልብ መመልከታቸው የቴሌን ገቢ በብዙ መልኩ የሚቀንስ ነው።
አንዳንዴም በፀረ ሽብር አዋጁ የተከለከሉ አመፅ የሚያስከትሉ መልዕክቶችን ከመለዋወጥም አልፎ በህልማቸው አመፁን
እያቀጣጠሉ የሚያድሩ እንዳሉም በርግጠኝነት እናገራለሁ። ይህም ትልቅ የሀገር ደህንነት ስጋት መሆኑን አምናለሁ።
ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን የሀገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች በህልማቸው እየተፈፀሙ መሆኑ የታወቀ
ወይም የተገመተ ከሆነ ግለሰቦች በድብቅ ህልማቸውን ለመበርበር በሚያስችል ፈቃድ በመታገዝ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ
እንዲቻል፤ ቅጣቱም ዳግም ህልም በዞረበት እንዳይዞሩ የእድሜ ልክ እንቅልፍ ማጣት ውሳኔ እንዲሆን እጠይቃለሁ።
በነገራችን ላይ ከኛም የባሱ ለመንግስታችን አሳቢ የሆኑ ግለሰቦች ፊልም ላይ ክልከላ ማድረጋቸውን በቅርቡ
ሰምቻለሁ። ይህም በጣም የሚያስመሰግን ነው። በኤድናሞል ሲኒማ ሲታይ የነበረው “ዲክታተር” የተባለ የፈረንጆች ፊልም
ክልከላ ለዚህ ማሳያ ነው። ነገሩ የሚበረታታ ቢሆንም፤ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም ህብረተሰቡ ፊልም ቢከለከል
ከሽብር ጋር የተያያዘ ህልም እያየ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነውና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አያይዤ አቤት
እላለሁ!
ከሰላምታ ጋር! (ልበል እንጂ…!)
እስቲ ወዳጄ ጥሩውን ጊዜ ያምጣልን!
አማን ያሰንብተን
Subscribe to:
Comments (Atom)